Organization background
United for Life Ethiopia was born out of a deep concern for the growing challenges facing Ethiopian families and communities. In a time when life is increasingly undervalued, we exist to be a counter-cultural voice — one that declares the worth of every human being from the very beginning of life to its natural end.
We exist to bring hope, compassion, and practical support to individuals and families facing difficult circumstances. Through advocacy, education, and community outreach, we empower people to choose life, dignity, and a hopeful future.
Dr. Seyoum Antonios
የዶ/ር ስዩም መልዕክት
“የጨለማው አጀንዳ በማያሻማ ሁኔታ ግልፅ ሆኖ ወጥቶአል!!”
የዛሬዋ ቀንና ይህ የሳምንት መጨረሻ ለኔና ለቤቴ እንዲሁም የጌታችን መንግስት ጉዳይ ግድ ለሚላቸው በጎ ፈቃድ ላላቸው ወገኖች ሁሉ በሌላ የልብ ስብራት ውስጥ ሆነን እያለፈ ያለ ጊዜ መሆኑን ስገልጥ በብዙ የሃዘን ስሜት ነው።
ጉዳዩ እንዲህ ነው
ይህ የሳምንት መጨረሻ ማለትም ከመጋቢት 25 እስከ 27/ 2018 ዓ/ም ያለውን ጊዜ በዓመት ውስጥ በበርካታ ሥፍራዎች “ቅድስና ለእግዚአብሔር!” በሚል ርእስ ወሲባዊ ቅድስናን አስመልክቶ በጌታ ፀጋ የምናካሄዳቸው ትምህርታዊ ኮንፈረንሶች መካከል አንዱ የሆነውንና “በዳዬ በንሳ” በምትገኘው “ሻሎም መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን” ከዘጠኝ ወራት በፊት ቀጠሮ የተያዘለትን ኮንፈረንስ ለማካሄድ የቀጠርንበት ጊዜ ነበር። የቤተ ክርስቲያኒቱ የወጣት አገልግሎት መሪዎች ለዚህ ኮንፈረንስ መሳካት ምን ያህል እንደደከሙ እኔ በግሌ ምስክር ነኝ። በተለይ ያለፈውን የአንድ ወር ጊዜ ፕሮግራሙን የተሳካ ለማድረግ ምን ያህል ደጋግመው እንዳሳሰቡኝ አልረሳውም:: እኔም በግሌ በብዙ ናፍቆት የምጠብቀው ፕሮግራም ነበር::
ይሁንና ያለፈው ሰኞ ከሌላ ተመሳሳይ ጉዞ በመመለስ ላይ እያለሁ ከወጣት መሪዎች አንዱ ወንድም ዘንድ ደውዬ ወደ ዳዬ የማደርገውን ጉዞ ዝግጅት በሚመለከት ሳናግረው እርሱ ግን ከቤተክርስትያኒቱ መሪዎች ጋራ በዚያን ቀን ያደረጉትን ውይይት ሀሳብ ጭብጥ በተረበሸ መንፈስ አካፈለኝ :: ይኸውም የመሰረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወሰዱ የተባለውን የመሰረዝ እርምጃ ተከትሎ ከተፈጠረው ሁኔታ የተነሳ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ እኔ ማገልገል እንደማልችልና ሌላ አገልጋይ መመደብ እንዳለበት ከደቡብ ሲኖዶስ የመጣ ደብዳቤ ማሳሰቡን መሪዎች እንደነገሩአቸው ነበር የነገረኝ :: ይህ ያልታሰበ ሁኔታ የወጣት መሪዎቹን ምን ያህል ሊረብሻቸው እንደሚችል መገመት አያዳግትም :: በዚያን ወቅት ኮንፈረንሱ ሊካሄድ የሦስት ቀናት ጊዜ ብቻ ቀርቶት ነበርና::
ነገሩን ለማሳጠር
በማግስቱ ማለትም ማክሰኞ ባደረጉት ድጋሚ ስብሰባ ወጣቶች የተቻላቸውን ያህል ከባድ ጥረትን ቢያደርጉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ከመጡባቸው ጫናዎች የተነሳ የኔን አገልግሎት ለመሰረዝ መገደዳቸውን ከቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች መካከል አንድ ወንድም ደውለው ነግረውኛል :: ይህም ለምን እንደሆነ ስጠይቃቸው ምክንያቱ ከዋናው መሰረተ ክርስቶስ ቢሮ ለደቡብ ኢትዮጵያ ሲኖዶስ በተላከ መልእክትና ያን ተከትሎም ሲኖዶሱ ወደ እነርሱ ከጻፈው ደብዳቤ የተነሳ በተጨማሪም በዳዬ ካለው የአብያተ ክርስቲያናት ህብረት ከካውንስሉም ቅርንጫፍ በመጣ ጫና መሆኑን አስረድተውኛል :: በአቋማቸው ከቀጠሉም ከመሪነት የመታገድ ውሳኔ ሊጠብቃቸው እንደሚችል ነገሩኝ :: በመሆኑም በአጭሩ ኮንፈረንሱ ሁለት ቀናትብቻ ሲቀሩት ሌላ አገልጋይ ፍለጋ ተገባ :: ይሁንና አሁን በደረሰኝ መረጃ መሠረት ፕሮግራሙ ዓርብም ቅዳሜም መካሄድ አልቻለም ::
በሆነው ሁሉ እጅግ ከማዘን በቀር አልተደነቅሁም:: ለምን ሲባል ከቀናት በፊት የነበረኝ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፈሎሺፕ ኮንፈረንስ እንዳይካሄድ በዋናው መሰረተ ክርስቶስ ቢሮ ተመሳሳይ ርብርብ መካሄዱን ኮንፈረንሱ ካለቀ በኋላ ከፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ሰምቼ ስለነበር :: ይሁንና የፌሎሺፑ መሪዎች የሆኑ ተማሪዎች ልክ በባህር ዳር ፈሎሺፕ እንደሆነው በወሰዱት ቆራጥ አቋምና ርምጃ የተነሳ ፕሮግራሙ ሳይስተጓጎል መካሄዱን ነግረውኛል ::
ይህ ብቻም አይደለም!
ከአንድ ወር በፊት በአዋሳ ካቦድ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ለወጣቶች እንዳስተምር ተጋብዤበት የነበረውን ፕሮግራም በሃዋሳ የመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ክልል ቢሮ ፀሐፊ ግፊት እንዲሁ መሰረዙን ያላወቁ በርካታ ወጣቶች በብዙ ጉጉት ወደ ፕሮግራሙ መጥተው በሃዘን መመለሳቸውን ሰምቻለሁ :: ይህን ስመለከት በዚህ ወሲባዊ ርኩሰት እንደሰደድ እሳት ሆኖ በቤተ ክርስትያን ውስጥ ሳይቀር ትውልድ እየበላ ባለበት ጊዜ የቅድስና ወንጌል እንዳይሰበክ ያውም የቤተ ክርስቲያን መሪ ነን በሚሉ አካላት ይህን ያህል ርብርብ መካሄዱ የጨለማውን ዓለም አጀንዳ አስፈጻሚ ሆነው መገለጣቸውን በግልፅ ያመለክታል ::
በቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ላይ የተቀመጡ ጥቂት ግለሰቦች እግዚአብሔርን ባለመፍራት በበቀልና በማናለብኝነት መንፈስ ተነሳስተው የቤተክርስቲያኒቱ መተዳደርያ ደንብና ውስጠ ደንብን ፈፅሞ በጣሰ ሁኔታና የአጥቢያ ቤተክርስቲያንን ሥልጣን በመናቅ እኔና ወንድሞቼን ከአባልነት ሰርዘናል የሚል “ውሳኔ” አሳልፈናል ማለታቸው ሳያሳፍራቸው በዚህ ልክ የቅድስና ወንጌል ጠላቶች ሆነው መነሳታቸው ተልኮአቸውን ግልፅ አድርጎታል:: እኔና ወንድሞቼ ከጌታ የተቀበልነውን አገልግሎት ባለመፈፀማችን የሚጠቀመው ጠላታችን ሰይጣንና አገልጋዮቹ ብቻ እንጂ ሌላ አይደለም::
ለነገሩማ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ከአሜሪካ ጉዞአቸው መልስ በፃፉት ሪፖርት ቁጥር ስምንት ላይ “:ግብረሰዶምን በመቃወም ኢላማ አጀንዳውን ወደ ቤተ ክርስትያን ያስገባሉ…. በቤተክርስቲያን መድረኮች ላይ ስለ ግብረሰዶም ከሚያስተምሩ ሰዎች መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው ::” ብለው መልዕክት ያስተላለፉ ቀን ነበር አጀንዳው ግልፅ ሆኖ መውጣት የጀመረው::
ትውልድ በሲቃ ውስጥ ሆኖ በኃጢአት ጦር እየተወጋ የአባት ያለህ የእናት ያለህ እያለ በመቃተት ወደ ሞት እየተነዳ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የጽድቅን ወንጌል ለማድረስ በመትጋት ፈንታ እነርሱ ለማይቆጠር ጊዜያት የሻሩትንና የረገጡትን መተዳደሪያ ደንብና መመርያ ተጥሶአል በሚል የሐሰት ክስ እውነተኛውንና ነፃ አውጭውን የቅድስና ወንጌል ‘ዓላማችን ወንጌል ነው?!” በሚል የማታለያ ካባ ተሸፍነው በአደባባይ በግልፅ ሲዋጉት በዓይኖቻችን አየን:: የእረኝነትና የደጋግ መጋቢነት ትርጉሙ የጠፋባቸውን ያህል የወንጌል ትርጉሙ እንደጠፋባቸው የገዛ ራሳቸው ምስክሮች ሆነው ተገልጠዋል ::
እነዚህ ግለሰቦች ግብረሰዶማዊያንን አቅፈው ከያዙት እንደ Mennonite World Conference (MWC) ያሉ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተለዩ መባላቸው እጅግ ስላበሳጫቸው ከግብረሰዶም አቃፊ ማህበራት ጋር በሚያደርጉት ሕብረት የሚያገኙት የግል ጥቅምና የዓለም አቀፍ ጉዞ ዕድሎች ይስተጓጎልብናል በሚል ስሜት የቅድስና ወንጌል እንዳይሰበክ፣ በእንደነዚህ ዓይነት ፕሮግራሞች በእግዚአብሔር መንፈስና በቃሉ ኃይል ወጣቶች ነጻ እንዳይወጡ፣ ትውልድ እንዲጠፋ… የግብረሰዶማዊነት አጀንዳ መግቢያ በር ሆነው የጨለማውን ኃይል ተልዕኮ በትጋት በመፈጸም ላይ ናቸው፡፡ ስለሚድኑ ነፍሳት፣ በእስራት ውስጥ ስላሉ ወጣቶች፣ እየተበተኑ ስላሉ ትዳሮች፣ እየፈረሱ ስላሉ አጥቢያዎችና ከቤተክርስቲያን እየጠፉና እየሸሹ ስላሉ ምዕመናን ግድ የማይሰጣቸው፣ የቀንና ሌሊት ሕልማቸው ስልጣንና ጥቅማቸው ብቻ መሆኑን የጌታ ህዝብም ሆነ የአጥቢያ ቤተክርስቲያናት መሪዎች ተገንዝበው ቤተክርስቲያናችንን ከእነዚህ መንፈሳዊ ካባ ከለበሱ ግለሰቦች ተጽዕኖ ሊጠብቁ ይገባል፡:
እነዚህ በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች የፈጸሟቸውን እጅግ ከባድ ጥሰቶች ተከትሎ ለእግዚአብሔር ህዝብ ከተነገሩ በርካታ ውሸቶች የተነሳ እንዲሁም ፍትህና ተጠያቂነትን አሽቀንጥረው በመጣላቸው ሊታገዱ የተገባቸው ሰዎች እንደሆኑ እውነታውን ዓለም ሁሉ አውቆት ሳለ እንዲሁም ገና ብዙ የሚገለጥ ጉድ ባለበት ሁኔታ አጥፊው ወገን ጥፋቶቹን ለመደበቅ በእንዲህ አይነት ቁርጠኝነት የቤተ እምነት አጥርን ሳይቀር ሰብሮ አልፎ በጌታ ቤት ውስጥ ስደትን ሲያፋፍም ከማየት የበለጠ አሳፋሪና አንገት የሚያስደፋ ክስተት ያለ አይመስለኝም ::
በአንፃሩ ግን እንዲህ ዓይነቱን የዓመጽ ግፊያ በቁርጠኝነት ተፋልመው አደራ ለተሰጣቸው መንጋ በመራራት የፅድቅን ወንጌል እንዲመገብ በእውነትና ስለ እውነት ዋጋ የከፈሉትን መሪዎች ከሁሉ በፊት የአጥቢያችንን ማለትም የለቡ አጥቢያ መሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ውድ የሆኑ መሪዎቿን አገልጋዮችና አባላትዋን በመቀጠልም የአዋሽ አርባ ሙሉወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን መሪዎችን አገልጋዮችና ምእመናንን ከባለቤቴ ሣቢ ጋራ በጌታ ስም እጅግ እጅግ አድርጌ ላመሰግን እወዳለሁ::
በተጨማሪም የጅማ ዩኒቨርስቲ ቴክኖ ካምፓስ ተማሪዎች ፈሎውሺፕ መሪዎችን፣ የባህር ዳር ሙሉወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን መሪዎችንና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፈሎውሺፕ መሪዎችን ፣ እንዲሁም የአምቦ ሙሉወንጌል፣ የወንዶገነት ሙሉወንጌል አማኞች አጥቢያ ቤተክርስቲያናት መሪዎች አገልጋዮችና አባላትን በውዱ ጌታችን ሥም እጅግ የከበረ ምስጋናችንን ሳላቀርብላችሁ ማለፍ አልወድም :: በክፉ ጊዜ ለእዉነት መቆም ምን ማለት እንደሆነ ዋጋ ከፍላችሁ በጀግንነት በመላው ዓለም ፊት መስክራችኋልና ዋጋችሁ እጅግ ታላቅ ነው:: ገድላችሁ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ በደማቁ ተጽፎ ይኖራል :: እኛም እጅግ እጅግ ኮርተንባችኋል::
ውድ ወገኖቼ!
አንድ ግልጽ ሆኖ ሊታወቅና ሊሰመርበት የሚገባ እውነት የዛሬው የመሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፈተናና አደጋ የመላው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አደጋ እና ፈተና መሆኑን ነው!! ዛሬም ቢሆን የምንወዳት ቤተክርስቲያናችን ግብረሰዶማዊያንን አቃፊ ከሆነው MWC ከተባለው ማህበር ፈጥና ትውጣ እንላለን፡፡ እስከ ዛሬ ቤተክርስቲያናችን የዚህ የሰይጣን ማህበር አባል ሆና መቀጠሏ ለተወሰኑ መሪዎች የግል ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆንም ቤተክርስቲያናችንን በእጅጉ አንገት ያስደፋና ያዋረደ ከሁሉም በላይ የአምላካችንን የእግዚአብሔር ስም ያሰደበ የወንጌልን እንቅፋት በመሆኑ እያንዳንዱን አባል፣ አገልጋይ፣ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን መሪዎችን ሊያንገበግብ ይገባል! ቤተክርስቲያናችን ከዚህ ማህበር አባልነት እስከምትወጣ፣ ለማገልገል የተሰጣቸውን ሥልጣን ለግል ክብርና ጥቅም እያዋሉ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ እየተጠቀሙ፣ ለጨለማው መንግስት አሰራር መንገድ እየጠረጉና ንጹሐንን እያሳደዱ ያሉ ግለሰቦች ከክፉ ስራቸው ተመልሰው ተጠያቂ እስኪሆኑ ድረስ መንፈሳዊ ተጋድሎአችንን እንቀጥላለን፤ ከዚህ ሌላ ዓላማ የለንም፡፡
በተጨማሪም በዚህ የጥፋት መንገድ ላይ እየሄዱ ላሉ መሪዎች የትዳር አጋሮች መልእክት አለኝ :: ምነው እንደዛች ልባም ሴት እንደ አቢግያ በመልካም ምክርና በጸሎት ባሎቻችሁ በጭካኔ ከያዙት ክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ ዋጋ ብትከፍሉ? ይህ ባለመሆኑ ነገ በቤታችሁ በትዳራችሁና በልጆቻችሁ የምትከፍሉት ብርቱ ዋጋ እንዳለ ማን በነገራችሁ? አሞፅ 7:13-17
የኔ ጌታ ግን እጅግ ያዘነውን ልቤን እንደልማዱ ባልጠበቅሁት መንገድ አፅናናኝ :: ከዳዬ ወጣት መሪዎች መካከል አንዱ እንዲህ ዓይነት ልብ የሚያነሳ መልእክት በዚያው ቀን ላከልኝ:: እንዲህ ይነበባል ::
“ዶክ እኔም በሰማሁት ውሳኔ ልቤ ተሰብሯል።
ላረጋግጥልህ የምፈልገው ነገር ግን ጠላት ሰዎችን ተጠቅሞ አገልግሎትህንና ለጌታ ያለህን ትጋት ለማወክ የተሳካለት ቢመስለውም፣ እንዲያውም ብዙ ወጣትን ለጌታ ለመቀደስ እና ርኩሰትን ከአንተ እና ከቃሉ ጎን ሆኖ እንዲዋጋ አነሳስቷል። ጠላትን “ቅድስና ለእግዚአብሔር” በሚል የሕይወት መታወቂያ እንበቀለዋለን። ብዙ ትውልድ ከጎንህ ነን። ለቤቱ ያለህን የቅድስናን ረሀብ አጋብተህብናል። እንከተልሀለን። አንተን ያስቆሙ መስሏቸው ብዙ ሌሎች የቅድስና ሠባኪዎች እንድንነሳ አድርገውናል። ዶክዬ አልከሰርክም፣ ሳትሰብክም በሕይወትህና ለጌታ ባለህ ቅናት ተማርከን ወደ ጌታ አይተናልና፣ ተሳክቶልሐል። ከልብ እንወድሃለን ”
እንደዚህ ወጣት ብዙዎቻችሁ በጸሎትም ሆነ በሚያበረታታ ቃል ከጎናችን ስለቆማችሁ ምስጋናችን ከልብ ነው! ድሉ የጌታ ነው!
ሁሉ በርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳችስ እንኳን ያለእርሱ አልሆነምና ክብር ሁሉ ከዘለዓለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ብቻ ይሁን!!
ይህንን ከጌታ የተቀበልነውን የቅድስናን ወንጌል የመስበክ አደራ የዓመፅ ግፊያው እያየለ መሆኑን እያየንም በጌታ ፀጋ ላይ ታምነን በቁርጠኝነትና በጭካኔ እስከመጨረሻዋ እስትንፋሳችን ድረስ በትጋት እንቀጥለዋለን ::
“ብርሃን በጨለማ ይበራል ጨለማም አያሸንፈውም ( Lux lucet in tenebris!!)” ዮሐንስ 1:5
መቼም ቢሆን ጨለማ ብርሃንን አሸንፎት አያውቅም!!! ስለዚህ በጌታችን ኃይል እንበረታለን!! ድል በድል እንሄዳለን….
በተረፈ ነገሮች እምን ደረጃ ላይ ደርሰው ይሆን ብላችሁ ለምትጨነቁ በሃገራችንና በዓለም ዙሪያ ላላችሁ ቅን የጌታ ልጆች ሁላችሁ ያለኝ መልእክት ጌታ አሁንም በሥራ ላይ ስለሆነ ልባችሁ ፈፅሞ እንዳይወድቅ እንድትበረቱ ነው :: ይሁንና ከሁለቱ የአዲስ አበባ ክልሎች የተውጣጡ መሪዎች መፍትሄን የማምጣት ሥራ እየሰሩ ስለሆነ የእነሱን ምላሽ እየጠበቅን ነው ተብሎ በዋና ቢሮም ሆነ በራሳቸው በመሪዎች የሚነገረው ማደናገሪያ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ መግዢያና ማዘናጊያ መሆኑን እንድትገነዘቡና እንዳትታለሉ በብርቱ ማሳሰብ እወዳለሁ ::
ይህ ስብስብ በዋናው ቢሮ ተልዕኮን ተቀብሎ የቢሮውን ሃሳብ ለማስፈፀም የሚተጋና ፍፁም ገለልተኛ ያልሆነ ገና ከጅማሬው ውጤት አልባ የሆነ ቡድን መሆኑን ማረጋገጥ እወዳለሁ:: የለቡ አጥቢያ አካዉንት የተከፈተው አባላቷ ለዋናው ቢሮ የሕግ ማስጠንቀቂያ በመስጠታቸው እንጂ በዚህ ቡድን ጥረት ወይም የዋናው ቢሮ ፍላጎት ሆኖ አይደለም :: የመሰረተ ክርስቶስ አስተዳደር መሪዎች (መአመጉ) ቤተክርስቲያናችን ላለችበት እጅግ አሳሳቢ ቀውስ እኛን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት የቀረበለትን አቤቱታና ጩኸት ጆሮ ዳባ ብሎ አንድም የመፍትሄ አቅጣጫን ሳያስቀምጥ እንደተለመደው የሁለት ሰዎችን ሃሳብ ሰምቶና አሜን ብሎ ምንም ላይፈይድ ለሦስተኛ ጊዜ ተሰብስቦ መበተኑን በዓይናችን አየን :: ነገ በሰውም ከሁሉም በላይ ደግሞ በጌታ በብርቱ የሚጠየቅበት ኃላፊነት መሆኑን እያንዳንዳቸው አባላቱ መቼ ይረዱ ይሆን? በዚህ ወሳኝ ወቅት የተሰጠውን ኃላፊነት ተጠቅሞ የመሪዎች ጠቅላላ ጉባኤን በአስቸኳይ መጥራት ሲገባው የተነገረውን ከእውነት የራቀ ሪፖርት ሰምቶ በመበተን ታሪክ የማይረሳው ታላቅ ስህተትና ጥፋት ሰርቶ አልፏል::
ስለዚህ የመፍትሄው ብቸኛ ምንጭ ወደ ሆነው ወደ ጌታ አምላካችን በአንድነት እንድንጮህ በታላቅ አክብሮት እማፀናለሁ። ማዳን የእርሱ ናትና!!
ክብር ለአብ ክብር ለወልድ ክብር ለመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ከዘለአለም እስከ ለዘለአለም ይሁን :: አሜን!!
በጌታ ወንድማችሁ ሥዩም አንቶኒዮስ ነኝ!
